አአዩ በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የአቋም መግለጫ አወጣ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላት በዛሬው እለት በመሰባሰብ በኢትዮጵያ እየታየ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋል የጋራ የአቋም መግለኛ በማንዴላ አደራሽ አቅርቧል፡፡

የአአዩ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና የአቋም መግለጫውን በሚከተለው መልክ በንባብ አሰምተዋል፡፡

አአዩ የእውቀት በር በመክፈት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ውለታ ያልዋለለት ኢትዮጵያዊም ሆነ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ምሁር ወይም ፕሮፌሰር የለም፡፡

አያሌ የቀድሞ ተመራቂዎቻችን በመላው ዓለም የሽብር ቡድኑን ድርጊት በማውገዝ ምዕራባዊያን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሲያወግዙ ተመልክተናል፡፡

ጥቂት ግለሰቦች ደግሞ ይህን የዩኒቨርሲቲውን የሀገር ውለታ ክደው ከሀገር አፍራሽ ሽብርተኞች ጋር ሲተባበሩ በሀገር ላይ ክህደት በመፈፀም በሚስጥርሚ ሲያሴሩ ተደርሶባቸዋል፡፡

እነዚህ አካላት ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እያስጠነቀቅን ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ዲግሪያቸውን እስከመንጠቅ የሚደርስ ህጋዊ እርምጃ ዩኒቨርሲቲው የሚወስድ መሆኑን እናሳስባለን፡፡

ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ውለታ ያለባችሁ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ይሁን የአሁን ምሁራን የጀመራችሁትን ሀገር የማዳን ትግል ዩኒቨርሲቲው የሚደግፍ መሆኑን አውቃችሁ እስከመጨረሻው ድረስ እንድትፋለሙ ጥሪየን አቀርባለሁ፡፡

ስለሆነም

1ኛ. እኛም ከፊትም ከኋላም ተሰልፈን መሪያችንን ተከትለን እስከ ግንባር ድረስ እንዘምታለን፡፡

2ኛ. የዩኒቨርሲቲዎች ዋነኛ አላማቸው የህብረተሰቡን ሰላምና ልማት ማረጋገጥ እንጂ ማደፍረስና ከሽብርተኞች ጋር መተባበር ባለመሆኑ አንዳንድ ምሁራን ከዚህ ድርጊታችሁ በመታቀብ ሀገር የምትጠብቅባችሁን የቁርጥ ቀን ውለታ እንድትወጡ አሳስባለሁ፡፡

3ኛ. አአዩ የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ የያዘውን የተዛባ ግምገማና አላስፈላጊ የውስጥ ታልቃ-ገብነት በፅኑ ያወግዛል፡፡

4ኛ. በታላላቅ የዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን ቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ አልጀዚራ፣ አጃንስ ፍራንስ ፕሬንስ በመሳሰሉት የሚሰራጨውን የሀሰት ዜና እናወግዛለን፡፡

5ኛ. አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት አሸባሪውን ህወሓትን በግልጽ ስለሚደግፉ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እናሳስባለን፡፡

6ኛ. የአሜሪካ ህዝብና መንግስት በተሳሳተ መረጃና ሆን ተብሎ በሚቀነባበር ሴራ ኢትዮጵያን ለማዳከም፣ አሸባሪውን ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት በጥልቀት እንዲያስቡበት እንመክራለን፡፡

7ኛ. ለአንድ ሀገር ሉአላዊነት፣ ነጻነትና ፍትህ ለሚታገሉ ለዓለም ዓቀፍ ማህበረሰቦችና ሀገራት ለእውነተኛው ትግላችን “በቃ” ብለው ደጋፋቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

8ኛ. መላው የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት፣ በአድሏዊ ማዕቀብና በሽብርተኝነት ላይ ጠንካራ ተቃውሞውን እንዲያሰማና ከእኛ ጋር በጋራ እንዲቆም ጥሪ እናቀርባለን፡፡

9ኛ. የአአዩ ማህበረሰብ የህልውና ዘመቻውን ከግቡ ለማድረስ የመንግስትን ጥሪ በሙሉ ተቀብለን አስፈላጊ ከሆነ ግንባር ድረስ ለመዝመት ዝግጁ ነን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ!

የአአዩ ማህበረሰብ

Image
Image